Mettu University Celebrated Employees' Day
 Published Date: Sep 25, 2026
Share:

መስከረም 14/2019 ዓ.ም (ህዓአግ) — የመቱ ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች ቀን “የዩኒቨርሲቲያችን ስኬት በጋራ አስተዋጽኦ!” በሚል መሪ ቃል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ።

የሥነ-ሥርዓቱን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዓለሙ ዲሣሣ በ2018 ዓ.ም የሥራ ዘመን በመማርና ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ታቅደው በስኬት የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በ2018 ዓ.ም ታቅደዉ በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጸሙ ያልቻሉ ሥራዎችን በቀጣዩ የሥራ ዘመን ለማጠናቀቅ አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል። በ2018 ዓ.ም የተመዘገቡት ስኬቶች የሁሉም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና መምህራን የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተሳትፎአቸውም ምስጋና አቅርበዋል።

በመቀጠል የ2018 ዓ.ም የሥራ ዘመን የአፈጻጸም ሪፖርት በስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ላቀው ቀርቧል።
በሪፖርቱ በመማርና ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች በዝርዝር ቀርበዋል።

በትምህርት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው ለመቀበል ካቀደው የተማሪ ቁጥር 85 በመቶ ያህሉን መቀበሉ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት መሰራቱ፣ የሀገር አቀፉን የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮጀክት ለማሳካት የተከናወኑ ሥራዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ሥልጠናዎች ከታቀደው 88 በመቶ ያህሉ መሰጠታቸው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የትምህርት ፕሮግራሞችን ዕውቅና (Program Accreditation) ለማስገኘት የተሰሩ ሥራዎችና የሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና (Exit Exam) የተማሪዎች የማለፊያ ምጣኔ መሻሻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በጥናትና ምርምር ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማካሄዱ፣ 500 ሺህ ያህል የተሻሻሉ ዝርያ ችግኞች መባዛታቸው፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት መቻሉ እና የባህላዊ መድኃኒት ጥናቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ተገልጿል።

በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በኢሉ አባ ቦርና በቡኖ በደሌ ዞኖች ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ቀጣይነት ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱ፣ ለት/ቤቶችና ተማሪዎች የትምህርት ግብዓት ድጋፍና ዕድሳት መደረጉ፣ ለአቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ መሰጠቱ እና ነጻ የሕግና የጤና አገልግሎቶች በስፋት መሰጠታቸው ተጠቅሷል።

በሪፖርቱ በዩኒቨርሲቲው ግቢና ከግቢ ውጭ በመካሄድ ላይ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችም ተካተዋል። በዩኒቨርሲቲው ግቢ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ማዕከል ግንባታ፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም ከግቢ ውጭ በሁሩሙ ወረዳ የኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ በመቱ ከተማ የዩኒቨርሲቲዉ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ግምባታና ሌሎች የልማት ሥራዎች ወደ ማጠናቀቂያ ደረጃ መቃረባቸው ተገልጿል።

በቀጣዩ የ2019 ዓ.ም የሥራ ዘመን እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለማጠናቀቅና አዳዲስ ተግባራትን ለመጀመር የተዘጋጀው የሥራ ዕቅድም በዝርዝር ቀርቧል።

በቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ላይ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዓለሙ ዲሣሣ፣ የአ/ም/ቴ/ሽ/ማ/አ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር በድሉ ተካ እና የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ረ/ፕ ጆን ተስፋዬ የተመራ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱም ከሠራተኞችና መምህራን ጥያቄዎች፣ ሀሳቦችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በመጨረሻም በ2018 ዓ.ም ከተቋማችን በጡረታ ለተሰናበቱ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተሰጥቷቸው፣ ለዓመታት ላበረከቱት አገልግሎትም ተመስግነዋል። 

We're dedicated to serve the community!

Gallery

Recent News

© 2026 Mattu University. All Rights Reserved.