🇪🇹 በመቱ ዩኒቨርሲቲ 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ተከበረ 🇪🇹
መቱ ዩኒቨርሲቲ | ጥቅምት 2፣ 2019 ዓ.ም
=============+==========
«ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን!» በሚል መሪ ቃል በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ የሚገኘው 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በመቱ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከብሯል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዓለሙ ድሳሳ፣ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ረ/ፕሮፌሰር ጆን ተስፋዬ፣ የአካደሚክ ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር በድሉ ተካ፣ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
በዕለቱ የክብረ በዓሉን መልዕክት አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዓለሙ ድሳሳ፣ ሰንደቅ ዓላማችን የሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን፣ የጋራ ማንነታችንና የሀገራዊ ኩራታችን ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ዓለሙ አክለውም፣ የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሀገሪቱ በውስጥና በውጭ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች ለመቋቋምና የሀገራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ በተለያዩ መስኮች ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ትርጉም እንዳለው አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሰንደቅ ዓላማችን ሥር በአንድነት በመቆም፣ የጋራ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካትና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ በትጋትና በኃላፊነት መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ሰንደቅ ዓላማን ማክበር ከሥነ ሥርዓቱ ተሳትፎ ባለፈ በሀገራዊ እሴቶች መጽናትን፣ ልዩነቶችን በመከባበር መቀበልን፣ ለጋራ ዓላማዎች በትብብር መሥራትንና ለሀገር እድገት የራስን ድርሻ መወጣትን ይጠይቃል።
መቱ ዩኒቨርሲቲም በትምህርት፣ በምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎትና በእውቀት ሽግግር የሀገርን ልማት በማገዝ፣ የአንድነት፣ የመግባባትና የጋራ ኃላፊነት እሴቶችን በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ውስጥ ለማጠናከር ያለውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የበዓሉ መልዕክት ያመለክታል።
ሰንደቅ ዓላማችን የጋራ ኩራታችን፣ የአንድነታችን ምልክትና የሀገራዊ መግባባታችን መሠረት ነው!